Top News Top News

Back

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የሀይቅ-ቢስቲማ-ጭፍራ የአስፋልት ኮንክሪት መንገድ ግንባታስራን ዛሬ በይፋ አስጀመሩ።

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የሀይቅ-ቢስቲማ-ጭፍራ የአስፋልት ኮንክሪት መንገድ ግንባታስራን ዛሬ በይፋ አስጀመሩ። 

በወረባቦ ወረዳ በቢስቲማ ከተማ ላይ በተካሄደው የፕሮጀክቱ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፣ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ፣ የብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ሀላፊ ብናልፍ አንዱአለም ።፣የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሃብታሙ ተገኘን ጨምሮ ከፍተኛ የፌደራልና እና የክልል የስራ ሃላፊዎች ታድመዋል።

መንግስት በመደበው ከ2 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የሚገነባው የሀይቅ- ቢስቲማ -ጭፍራ 74.3 ኪ. ሜ የአስፋልት ኮንክሪት መንገድ ግንባታ ፕሮጀክት የህዝቡን የአመታት ጥያቄ ምላሽ የሰጠ ነው ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ። ለረዥም ዓመታት የመንገድ መሰረተ ልማት ባለመኖሩ የዚህ አካባቢ ነዋሪ በከፍተኛ ሁኔታ ሲቸገር እንደቆየም ተናግረዋል። ይህ ታሪክ ሊሆን በመቃረቡ  ለመላው ህዝብ   የእንኳን ደስ ያላችሁመልክታቸውንአስተላልፈዋል።

 መንገድ መጀመር አንድ ትልቅ ምዕራፍ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ  ከተያዘለት ጊዜ በፊት  እንዲጠናቀቅ  የአካባቢው ነዋሪዎች እና የአመራር አካላት በብርታትና ጥንካሬ ከተቋራጮቹ  ጋር  በመሆን የሚያጋጥሙ የወሰን ማስከበር ችግሮችን ቀድመው እንዲፈቱም አሳስበዋል። የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ  ፕሮጀክቱ የህዝቦችን ጥያቄ ምላሽ የሰጠና ሀገራዊና ክልላዊ ፋይዳው የጎላ በመሆኑ የበኩላቸውን ድጋፋና ክትትል እንደሚያደርጉም  አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር  ኢንጂነር ሀብታሙ ተገኝ በበኩላቸው ተቋማቸው የሀይቅ-ቢስቲማ-ጭፍራ መንገድ ፕሮጀክትን  በስኬት ለማጠናቀቅ ተገቢውን የድጋፍ፣ የክትትል እና የቁጥጥር ሥርዓትን  እንደሚያደርግ  ገልፀዋል። መላው የአካባቢው ነዋሪ ፣የሥራ ተቋራጩም ሆነ የአማካሪ ድርጅቱ የተጣለባቸውን ከፍተኛ ሀላፊነት በብቃት እንዲወጡም  አስገንዝበዋል ።  የመንገድ ግንባታውን   ፓወርኮን ኃላ.የተ. የግል ማህበር እና አሰር ኮንስትራክሽን ኃላ.የተ. የግል ማህበር በሽርክና  በመሆን የሚገነቡት ነው።

የሀይቅ- ቢስቲማ -ጭፍራ ጠጠር መንገድ ለረጅም ጊዜ በአገልግሎ ሳቢያ በከፍተኛ ሁኔታ የተበላሸ ሲሆን መንገዱን ለመገንባት የሚወጣው  ሙሉ ወጪ በኢትዮጵያ መንግስት ይሸፈናል። አሁናዊው የመንገዱ ሁኔታ ከ 6 ሜትር  ያልበለጠ የጎን  ስፋት ያለውና ጠባብ ሲሆን  በእስፋልት ደረጃ ሲገነባ በወረዳ   19 ሜትር ፣ በቀበሌ 15ሜትር እንዲሁም  በገጠር 1ዐ ሜትር ስፋት ይኖረዋል፡፡ የመንገዱ ግንባታ በሚጠናቀቅበት ወቅት ከዚህ በፊት ከደሴም ይሁን ከሀይቅ ወደ ጭፍራ ለመሄድ በወልድያ በኩል በሚሌ-ጭፍራ ይደረግ የነበረውን የዙሪያ ጥምጥም ጉዞ በማስቀረት 

በአቋራጭ በቀጥታ ከሀይቅ በቢትሰማ አድርጎ ጭፍራ ዘመናዊ በሆነ መንገድ መጠቀም ስለሚያስችል የትራንስፖርት ጊዜን ከመቀነስ አኳያ ትልቅ ፋይዳ ያለው መንገድነው። እንዲሁም በመስመሩ የሚገኙትን ዞኖችና ወረዳዎች በቅርበት በማስተሳሰር ከዚህ ቀደም 74 ኪ.ሜትሩ ን በትራንስፖርት ለመጓዝ ይፈጅ የነበረውን አራት ሰዓት ከግማሽ በታች ያሳጥረዋል። ከዚህም ባለፈ   የቁም እንስሳት ውጤቶች ፣ፍራፍሬና ሌሎችንም ምርቶችን ወደገብያ አውጥቶ በመሸጥ አምራቾችንና ሸማቾችን የጋራ ተጠቃሚ ያደርጋል። ፕሮጀክቱ የውል ስምምነት መሰረት በአራት አመት ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል ።