Top News Top News

Back

የደብረብርሃን - አንኮበር አስፋልት ኮንክሪት መንገድ ግንባታ ዋና ዋና ሥራዎች ተጠናቀቁ

የደብረብርሃን - አንኮበር አስፋልት ኮንክሪት መንገድ ግንባታ ዋና ዋና ሥራዎች ተጠናቀቁ ::

አዲስ አበባ, የካቲት 4፣ 2016 (ኢመአ) ፡-  የደብረብርሃን - አንኮበር 42 ኪሎሜትር አስፋልት ኮንክሪት መንገድ ግንባታ ፕሮጀክት ዋና ዋና ሥራዎች የተጠናቀቁ ሲኾን፣ ቀሪ ውስን ሥራዎችን በአጭር ጊዜ ውስጥ ሙሉ በሙሉ ለማጠናቀቅ በትኩረት እየተሠራ ነው፡፡ አሁን ላይ ከግንባታው አጠቃላይ ሥራ 98 በመቶው ተጠናቋል። ከግንባታ ሥራዎች መካከል የ39 ኪሎሜትር የአስፋልት ንጣፍ ፣ የውኃ መፋሰሻ ቱቦ ፣ ሰብቤዝ ፣ የመንገድ ዳር የአደጋ መከላከያ አጥር እንዲሁም የትራፊክ ጠቋሚ ምልክቶች የማቅለም ሥራዎች ተከናውነዋል፡፡ሀገር በቀሉ ሰንሻይን ኮንስትራክሽን ግንባታውን እያከናወነ የሚገኘ ሲሆን ፣ የማማከርና የቁጥጥር ሥራውን ደግሞ ኮር ኮንሰልቲንግ ኢንጅነርስ በመሥራት ላይ ይገኛል፡፡ ፕሮጀክቱን ለማካሄድ የተመደበው 1,623,194,217.85(አንድ ቢልዮን ስድስት መቶ ሃያ ሶስት ሚሊዮን አንድ መቶ ዘጠና አራት) ብር በፌደራል መንግስት በጀት ነው የተሸፈነው። በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ውስጥ የሚገኘው ይህ መንገድ በጠጠር ደረጃ ተገንብቶ ላለፉት በርካታ ዓመታት አገልግሎት ሲሰጥ የቆየ ነው፡፡ ሆኖም ግን ከአገልግሎት ብዛት አኳያ መጎዳቱ ፤  የቦታው አስቸጋሪ ተፈጥሮአዊ አቀማመጥ በጠጠር ደረጃ ለነበረው የትራንስፖርት አገልግሎት አመቺ አለመሆኑ እንዲሁም ያለው በርካታ ሀገራዊ እና ማኅበራዊ ጠቀሜታ ከግምት ውስጥ ገብቶ በአስፋልት ኮንክሪት ደረጃ እየተገነባ ይገኛል፡፡  

ከዚሁ የደብረብርሃን-አንኮበር የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት በተጨማሪ የአንኮበር-ዱለቻ እና የዱለቻ-አዋሽ መንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች በመካሄድ ላይ ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ሶስት ፕሮጀክቶች ሙሉ ለሙሉ ሲጠናቀቁ ከዚህ ቀደም ወደ አፋር ለመሄድ ይወስድ የነበረውን ዙሪያ ጥምጥም ጉዞ ለማስቀረት እንደ አማራጭ ሆነው ያገለግላሉ፡፡ የአንኮበር ከተማ የተለያዩ ታሪካዊ ቅርሶችን በውስጡ የያዘው የአጼ ምኒሊክ ቤተመንግስት መገኛ በመሆኑ ፣ መንገዱን ለቱሪስቶች ምቹ በማድረግ በኩል ግንባር-ቀደም ሚና ይጫወታል፡፡ በተጨማሪም ምቹ የትራንስፖርት ፍሰት እንዲኖር በማስቻል የኅብረተሰቡን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ በእጅጉ የሚያቃልል ከመሆኑም ባሻገር ምርት በቀላሉ ወደ ማዕከላዊ ገበያ እንዲደርስ በማስቻል የአርሶ-አደሩን ተጠቃሚነት ይጨምራል፡፡

በተጨማሪ
› አጭር መልዕክት 8561
› ፖስታ ሳጥን ቁጥር 1770
› ድህረገጽ www.era.gov.et
› ፊስቡክ https://www.facebook.com/www.era.gov.et
› ቴሌግራም https://t.me/ethioroads
› ትዊተር https://twitter.com/EthiopiaRoadsAd
› ኢሜል communication@era.gov.et


what is new? what is new?