News News

ባለፉት ሁለት ዓመታት በሁሉን አቀፍ የገጠር መንገድ ተደራሽነት ፕሮግራም (URRAP) ከ11 ሺህ 450 ኪ.ሜትር በላይ መንገዶች ግንባታ ተካሔደ፡፡

ባለፉት ሁለት ዓመታት በሁሉን አቀፍ የገጠር መንገድ ተደራሽነት ፕሮግራም (URRAP) ከ11 ሺህ 450 ኪ.ሜትር በላይ መንገዶች ግንባታ ተካሔደ፡፡ በአጠቃላይ በፕሮግራሙ 90 ሺህ ኪ/ሜ መንገድ ለመገንባት ታቅዶ እየተሠራ ነው::የፕሮግራሙን ዕስካሁን አፈጻጸም የሚገመግምና የቀጣይ የትኩራት ኣቅጣጫዎች ላይ ያተኮረ ስብሰባ የሚመለከታቸዉ የበለድርሻ ኣካላት በተገኙበት በዛሬዉ ዕለት በሂልተን ሆቴል ተካሄደ፡፡

በሁለተኛው የትራንስፎርሜሽን እቅድ አገሪቱን ወደላቀ የእድገት ደረጃ ለማድረስ በመንግስት የተነደፈውን ሁሉንም የአገሪቱን ቀበሌዎች ደረጃውን በጠበቀ የመንገድ መረብ ከዋና መንገድ ጋር የማገናኘት ፕሮግራም(URRAP)ን  ስኬታማ  ለማድረግ በተደረገው ጥረት ባለፉት ሁለት ዓመታት (እስከ ሐምሌ 2009 ባለው ጊዜ ዉስጥ)ከ11 ሺህ 450 ኪ.ሜትር በላይ መንገዶች ግንባታ መካሔዱን የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን የኮሙኒኬሽን ዳይሬክቶሬት አስታወቀ*

በ2010 በጀት ዓመት በዚሁ ፕሮግራም የተያዘውን እቅድ ለማሳካት እንዲያስችል ባለሥልጣን መ/ቤቱ ክልሎችንና ሌሎች የባለድርሻ አካላትን ከማስተባበርና የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን ከማከናወን ጀምሮ ከፍተኛ የሆነ ርብርብ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ ለአምስት ዓመት የተያዘውን 90 ሺህ ኪሎ ሜትር መንገድ ግንባታ ለማሳካት በየዓመቱ ተሸንሽኖ በተቀመጠው እቅድ መሠረት በ2010 በጀት ዓመት 19,682 ኪ/ሜትር መንገድ በሁሉም ክልሎች ይገነባል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ 90 ሺህ ኪሎ ሜትር የመንገድ ግንባታ ሥራዎች ለማካሄድ በአጠቃላይ ከ45 ቢሊዮን ብር በላይ ይፈጃል ተብሎ ይገመታል፡፡      ከዚህም ውስጥ በመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ትግበራ ያልተገናኙ ቀበሌዎችን የሚያገናኙ እና በርካታ ህዝብና የጎላ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸውን መንደሮች (ቦታዎች) ከቀበሌና ወረዳ ማዕከላት ጋር የሚያገናኙ የገጠር መንገዶች ግንባታ ሥራዎች የአንበሳውን ድርሻ ሊወስዱ እንደሚችሉ ከግንዛቤ ተወስዷል፡፡ እነዚህ መንገዶች የገጠሩን ህብረተሰብ አኗኗርና አጠቃላይ ኑሮ ከመቀየር፣ የማህበራዊ አገልግሎቶችን ተደራሽነት ከማሻሻል፣ ድህነትን ለማስወገድ የሚደረገውን ጥረት ከማገዝ እና አጠቃላይ መዋቅራዊ ለውጥ ከማምጣት አኳያ የሚኖራቸው ፋይዳ እጅግ በጣም ከፍተኛ ነው፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ፕሮግራሙ በአነስተኛና መካከለኛ ደረጃ የተደራጁ አማካሪዎችና የሥራ ተቋራጮችን በብዛት በማፍራት ለወደፊቱ የአገሪቱ የኮንስትራክሽን ዘርፍ ጥንካሬና ተወዳዳሪነት መሠረት ይጥላል ተብሎ ይታመናል፡፡ በዚህም መሠረት በአገር አቀፍ ደረጃ በመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመን ብቻ በስራው ላይ የሚሳተፉ የአነስተኛ ተቋማት ከ1,200 በላይ ተቋራጮችና አማካሪዎች ነበሩ፡፡በመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን ህብረተሰቡ ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት የነፃ ጉልበትና ሌሎች ተሳትፎዎችን በማድረግ ለተመዘገበው ውጤት የራሱን ጉልህ ሚና የተጫወተ በመሆኑ ሊበረታታና ሊመሰገን ይገባል፡፡ ከዚህ በተጨማሪፕሮግራሙ በየዓመቱ በአማካይ እስከ 300 ሺህ ለሚደርሱ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድሎችን መፍጠር ችሏል፡፡በአጠቃላይ  ፕሮግራሙ ከመጀመሩ በፊት ክረምት ከበጋ በሚያስኬድ የመንገድ መረብ የተገናኙ ቀበሌዎች 40 በመቶ ብቻ የነበሩ ሲሆን፣ በመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን መጨረሻ በተደረገው ከፍተኛ ርብርብ ወደ 76 በመቶ ማድረስ ተችሏል*

በፕሮግራሙ በመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን 71,523 ኪሎ ሜትር መንገድ ለመገንባት እቅድ ተይዞ 46,810 ኪሎ ሜትር (የዕቅዱ 65 በመቶ) ማሳካት መቻሉ የሚታወስ ነው፡፡ፕሮግራሙ እስከ 2008 ዓ.ም መጨረሻ ለተመዘገበው 113,066 ኪሎ ሜትር አጠቃላይ የአገሪቱ የመንገድ አውታር ላይ የነበረው ሚና እና በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን የእቅድ ዘመን 215 ሺህ ኪሎ ሜትር ለማድረስ ታቅዶ በመተግበር ላይ ለሚገኘው የመንገድ ኔት ወርክ ላይ የሚኖረው ሚና ከፍተኛ ነው፡፡