News News

ከ869 ሚሊዮን ብር በላይ የተገነባው የጮሌ-ማኛ 20 ኪሜ አስፋልት መንገድ ግንባታ ተጠናቆ ለትራፊክ ክፍት ሆነ፡፡

በኦሮሚያ ብ/ክ/መ በአርሲ ዞን  የሚገኘውን  የጮሌ-ማኛ መንገድ ግንባታ በ869 ሚሊዮን ብር በላይ ያከናወነው ሲጂሲ ኦቨር ሲስ ኮንስትራክሽን ግሩፕየተባለው የቻይና አለም አቀፍ የስራ ተቋራጭ ድርጅት ሲሆን የምህንድስና ቁጥጥርና የማማከር ስራውን ያካሄደው  ሮድ ዲዛይን ኤንድ ዲቨሎፕመንት ኮንሰልታንት  ነው፡፡

ከአዲስ አበባ 248 ኪሜ ርቀት  ከጮሌ ከተማ አራት ኪሎ ሜትር ወጣ ብሎ የሚጀምረው የመንገዱ ፕሮጀክት  የግንባታው  አይነት ዲዛይን ግንባታ የሚሰኘው ሲሆን ይህም ተቋራጩ ደዛይን ስራን ከግንባታ ጋር  ጎን ለጎን የሚያካሂድበት ነው፡፡ ፕሮጀክቱ  ከዚህ ቀደም ምንም አይነት የመንገድ መሰረተ ልማት ያልነበረው  አዲስ መንገድ ግንባታ ነው፡፡

የጮሌ -ማኛ የአስፋልት መንገድ ለግንባታ የዋለው  መውአለ ንዋይ ሙሉ ለሙሉ በኢትዮጵያ መንግስት መሸፈኑ ተገልጸ*ል፡፡   የመንገዱ የጎን ስፋት 7 ሜትር ሲሆን በግራና በቀኝ 0.5 ሜትር  ትከሻ አለው ፡፡ የፕሮጀክቱ ግንባታ የተከናወነበት  ተፈጥሮአዊ መልክአምድር አቀማመጡ   ከዘጠና በመቶ በላይ  ተራራማ እና ገደላማ ቦታ ላይ ከመሆኑም ባሻገር ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ፣የመሬት መንሸራተት ግንባታውን ፈታኝ አድርጎታል ፡፡ ግንባታው ከፍተኛ የቆረጣ ስራ ፣ የአንድ ድልድይ እና ብዛት ያላቸው የውሀ መውረጃ ቦዮች እና የፉካዎች ግንባታን ያካተተ ነበር ፡፡

የመንገዱ መገንባት ነባሩ ከጮሌ ተነስቶ  ማኛ የሚዘልቀው መንገድ ለትራንስፖርት አመቺ ያልሆነ ከሁለት ሰአት በላይ የጉዞ ግዜ ይፈጅ ነበረ፡፡  በክረምት ወቅት ደግሞ ትራንስፖርት አገልግሎት ለብዙ ቀናት የሚቋረጥበት ግዜ ነበር፡፡  ይህ አሁን  በአዲስ መልክ የተሰራው አዲስ መንገድ ሁለቱን ከተሞች በቅርበት በማስተሳሰር  የጉዞ ጊዜውን ከ30 ደቂቃ በታች እንደሚያሳጥረው ይታመናል፡፡በአካባቢው የሚመረተውን ስንዴ ፣ገብስ፣ባቄላ እና  ፍራፍሬ እንዲሁም የቡናና የጫት ምርት ወደ መሃል ገበያ ለማድረስ ያግዛል ፡፡

የጮሌ-ማኛ አስፋልት መንገድ የተሽከርካሪ የጉዞ ጊዜና ወጪ በከፍተኛ ደረጃ ከመቀነሱም በላይ በቂ የሆነና ደረጃውን የጠበቀ የመንገድ መሠረተ ልማት የሌለውን የአካባቢው ሕብረተሰብ የመንገድ ተጠቃሚ አድርጓል ፡፡አንዱን አካባቢ ከሌላው ጋር በማሰተሳሰር የምርትና የሸቀጥ ልውውጥን ያለእንግልት በቀላሉ እንዲከናወኑም ይረዳል  ፡፡ ባጠቃላይ በመስመሩ ላይ የሰፈሩትን አርሶ አደሮች፣ አጎራባች ወረዳና ዞኖችም ጭምር ሁለገብ ጠቀሜታን ያሳድጋል ተብሎም ታምኖበታል፡፡

የጮሌ-ማኛ  መንገድም ሆነ የሌሎች መንገዶች መገንባት ባለሥልጣን መ/ቤቱ በእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ ዘመን ለማሳካት ያቀደውን የመንገድ ዘርፍ ልማት ኘሮግራም ዓላማዎች ማለትም አገናኝ መንገዶች መገንባት፣ከፍተኛ የትራፊክ ፍሰት ያላቸውን መንገዶች ማሻሻል፣ልማትን የሚከፍቱ አዳዲስ መንገዶች መገንባት፣ሕብረተሰቡን በገበያና ሌሎች ማህበራዊ አገልግሎቶች ተጠቃሚ ማድረግ፣አገራዊ የግንባታ ኢንዱስትሪውን ማሳደግ የሚሉት ግባቸውን እንዲመቱ ከማስቻሉም በተጨማሪ መንግሥት ለዘርፉ የሰጠውን ከፍተኛ የሆነ ትኩረት የሚያሳይ ነው፡፡

እንደሚታወቀው የመንገዱ ግንባታ ከፍተኛ መዋእለንዋይ የፈሰሰበት እንደመሆኑ መጠን መንገዱ የሚፈለግበትን አገልግሎት መስጠት ይችል ዘንድ በአካባቢው የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍልና የመስተዳድር አካላት የትራፊክ ምልክቶችን ድልድዮችን፣የውሀ ማስተላለፊያ ቱቦዎችን እና ከእርሻ ማሳ የሚወጡ ጎርፎችን ወደ መንገዱ አንዳይወጡ በመከላከል ትብብር እንዲያደርጉና  መስመሩን የሚጠቀሙ አሽከርካሪዎች አካባቢው ገደላማ እና ጠመዝማዛ በመሆኑ የትራፊክ አደጋ እንዳይከሰት በጥንቃቄ  መንገዱን እንዲጠቀሙና መንገዱ ላይ የተተከሉትን የትራፊክ ምልክቶች እንደራሳቸው ሀብት ሊጠብቁና ሊንከባከቡ እንደሚገባ የኢትዮጵያ መንገዶች ያሳስባል፡፡