News News

ወደ አሰብ ወደብ ምን እየተሰራ ነው? ምንስ ታስቧል?

ከአዲስ አበባ እስከ አሰብ 882 ኪሜ ርዝማኔ አለው፡፡ ከዚህም ውስጥ 811 ኪሜ በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ 71 ኪሎሜትሩ ደግሞ በኤርትራ ክልል ውስጥ ይገኛል፡፡ ቡሬ ከተማ በአሰብ መስመር የመጨረሻዋ የኢትዮጵያ ድንበር ከተማ ናት ፡፡

በምስራቁ የኢትዮጵያ ክፍል በአዲስ አበባ - አዋሽ - ሰመራን አልፎ በዲቼቶ እና በጋላፊ መካካል ወደ ግራ ተገንጥሎ የአሰብ መዳረሻ መንገድ እናገኛለን ፡፡ ከመገንጠያው እስከ ቡሬ ድረስ 142.5 ኪሜ ይረዝማል፡፡ መንገዱ አስቀድሞ ጣልያን ኢትዮጵያን በወረረች ግዜ እንደተገነባ ይነገራል፡፡ በመቀጠልም ሶጃ የተባለው የፈረንሳይ ተቋራጭ ድርጅት በአስፋልት ደረጃ መንገዱን ገንብቶታል፡፡

ሆኖም በ1990 ዓ.ም በሁለቱ ወንድማማቾች ሀገሮች መካከል በተነሳው ጦርነት ምክንያት የተሰራው መንገድ በቅጡ ግልጋሎት ሳይሰጥ ሊቋረጥ የግድ ሆነ፡፡ ሁለት አስርተ አመታት አለፉ ፡፡ በያዝነው አመት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ያደረጉት የሰላም ጥሪ ውጤት አስገኝቶ ሁለቱ ሀገራት ሁሉን አቀፍ ስምምነት ሊያደርጉ ቻሉ፡፡ ከዚህም ውስጥ የአሰብ ወደብን መጠቀም አንዱ አጀንዳ ነበር ፡፡ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ከመንግስት የተሰጠውን ሃላፊነት ተቀብሎ ኮሪደሩን ለመክፈት እንቅስቃሴ ጀምሯል፡፡

ለመሆኑ በባለስልጣኑ በኩል መስመሩን ለትራፊክ ምቹ እና አስተማማኝ ለማድረግ ምን እየተሰራ ነው? ምን ታስቧል የሚለውን ለማየት ያክል ፡፡ ከአዲስ አበባ ጅቡቲ ከሚወስደው ዋና መንገድ ጋላፊ ለመድረስ 4 ኪሜ ሲቀረው በኢትዮጵያ መንግስት ከ2.66 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ወደ አሰብ አቅጣጫ አድርጎ ማብቂያውን ኢትዮ - ጁቡቲ ድንበር በልሆ ላይ ከታጁራ ወደብ ጋር ለመገናኘት ያለመ አንድ የመንገድ ፕሮጀክት በግንባታ ላይ ይገኛል፡፡

የፕሮጀክቱ መጠርያ ስም ዲቼቶ ጋላፊ መገንጠያ-ኤሊዳር- በልሆ ይባላል፡፡ 78 ኪሜ ይረዝማል፡፡ ጥቅምት 2008 ዓ.ም ላይ ነበር በመከላከያ ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝ ግንባታው የተጀመረው፡፡ የግንባታው አይነት ዲዛይን እና ግንባታን በጋራ ያካተተ ሲሆን ከዚህ ቀደም ከለመድናቸው የአስፋልት መንገድ በተለየ በሲሚንቶ ኮንክሪት ደረጃ የሚገነባ ነው፡፡ መንገዱ ነባሩን የአሰብ ወደብ መንገድ በተወሰነ ደረጃ መስመሩን የተከተለ ቢሆንም ኤሊዳር ከተማ 64 ኪሜ ላይ ወደ ሰሜን ምስራቅ ታጥፎ 14 ኪሜ እንደተጓዘ የጅቡቲ ገጠር ቀበሌ ወደሆነችው በልሆ ያገናኛል፡፡ ፕሮጀክቱ በእስካሁኑ ካጠቃላይ ስራው 52 በመቶ ያህሉ የተጠናቀቀ ሲሆን ከዚህም ውስጥ 32 ኪሜ የሲሚንቶ ንጣፍ ስራው ተከናውኗል፡፡

የዚህ መንገድ መገንባት አዲሱን የታጁራ ወደብ ለመጠቀም የሚያስችል በመሆኑ በነባሩ ጅቡቲ ወደብ ይፈጠር የነበረውን የትራንስፖርት ጫና እስከ ሀምሳ በመቶ ያቃልላል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በሌላ በኩል የአሰብ የመንገድ ኮሪደርን ክፍት ለማድረግ በሚደረገው እንቅሰቃሴ ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ መንገዱን መጠቀም ስለሚያስችል የራሱ ጠቀሜታ ይሰጣል፡፡ ከዚህ ባሻገር ባካባቢው ያሉ የፖታሽ አውጪ ድርጅቶችን ካለምንም ውጣውረድ ወደ ገበያ ለማድረስ እንደሚያግዝ ይጠበቃል፡፡

ከላይ ከጠቀስነው ፕሮጀክት መገንጠያ 64 ኪሜ በመቀበል ወደ አሰብ የሚዘልቀው 71 ኪሜ ያህል ማንዳ ከተማን አልፎ የኢትዮ ኤርትራ ድንበር ከተማ ወደ ሆነችው ቡሬ ይደርሳል፡፡ በዚህ 71 ኪሜ መስመር ውስጥ ሁለት አይነት የመንገድ ደረጃዎች እናገኛለን ፡፡ የመጀመርያው የተጎዳ የጠጠር መንገድና ጥገና የሚፈልጉ ድልድዮችም እንዲሁም በጥሩ ይዞታ ላይ ያለ የአስፋልት ኮንክሪት መንገድ ነው ፡፡ በመሆኑም በዚህ አካባቢ ከሚከናወኑ ስራዎች መካከል የመንገድ ግራና ቀኝ ትከሻ የሌላቸውን የመስራት፣ የአስፋልት ንጣፍ ስራ ፣ሁለት ተሸከርካሪ በአንድ ግዜ ማስተናገድ የማይችሉትን ስፋት እንዲጨምር ማድረግ፣የተበላሹ ድልድዮችን መጠገን በአዲስ መልክ መገንባት የሚፈልጉትን ግንባታ ማከናወን ፣የውሃ መፋሰሻ ትቦና ቦዮችንና የትራፊክ ምልክቶችን የማስቀመጥ ስራም እንዲሁ ማከናወን ይገኝበታል፡፡

የአሰብ ኮሪደር ላይ የባለስልጣን መ/ቤቱ ዋና ዳይሬክተር ኢ/ር ሀብታሙ ተገኘን ጨምሮ የተለያዩ የስራ ሃላፊዎች በነሃሴ 2 ቀን 2010 ዓ.ም ከዲቼቶ ጀምሮ ቡሬ ድረስ ጉብኝት አድረገዋል፡፡ በዚሁም መሰረት በመከላከያ ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝ እየተሰራ ያለው መንገድ የግንባታ ሂደቱ ተፋጥኖ እንዲያልቅ ከኢንተርፕራይዙ የስራ ሃላፊዎች ጋር ተነጋግረዋል፡፡

ሌላው ጥገና የሚፈልገው እሰከቡሬ ያለውን መንገድ በቀጣይ ወደ አሰብ ወደብ የሚጓዙ የጭነት ተሸከርካሪዎችን ክብደት መሸከም እንዲያስችል ሆኖ የመንገዱን ደረጃ የማሳደግና ማስፋት ፣ የድልድይ ስራ ማስጀመር እንዲሁም መስመሩ ላይ ያሉ ቀጣይ የጥገና ሂደቶች ላይ ከመከላከያ ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝና ከኢትዮጵያ ኮንስተራክሽን ስራዎች ጋር ተነጋግረዋል፡፡