ዜና ዜና

Back

ኢንጂነር ሽመልስ እሸቱ የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደርን በዋና ዳይሬክተርነት ተረከቡ፤ ለማኔጅመንቱ የሥራ መመሪያና አቅጣጫ ሰጡ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 02 ቀን 2019 ዓ.ም (ኢመአ)፦ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር (ኢመአ) ዋና ዳይሬክተር ሆነው የተሾሙት ኢንጂነር ሽመልስ እሸቱ፣ ከቀድሞው ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር መሐመድ አብዱራህማን ጋር ይፋዊ የሥራ ርክክብ ፈጽመዋል።

በርክክብ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የቀድሞው ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር መሐመድ አብዱራህማን ባስተላለፉት መልዕክት፤ ተቋሙ ከመንግሥት የተሰጠውን ከፍተኛ ኃላፊነት በብቃት ከመወጣት አኳያ ውጤታማ ሥራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል። በቀጣይም የተቀመጡ ዕቅዶችን በሚጠበቀው ደረጃ ከማስፈጸም አኳያ የተቋሙ አዲሱ ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሽመልስ እሸቱ ከማኔጅመንቱ ጋር በቅንጅት እንደሚሰሩ ሙሉ እምነታቸውን ገልጸው፣ ለመላው የተቋሙ የሥራ ባልደረቦች ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የሥራ ርክክቡ ከተጠናቀቀ በኋላ፣ አዲሱ ዋና ዳይሬክተር በተቋሙ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ከተቋሙ አማካሪዎች፣ ምክትል ዋና ዳይሬክተሮች እና ከፍተኛ ዳይሬክተሮች ጋር የትውውቅና ቀጣይ የሥራ አቅጣጫ ማስቀመጫ መድረክ አካሂደዋል።

በመቀጠልም የኢመአን አጠቃላይ መዋቅር፣ የተቋሙን ተልዕኮና ራዕይ፣ በሂደት ላይ ያሉ ሜጋ ፕሮጀክቶችን እንዲሁም አጠቃላይ የሥራ እንቅስቃሴን የሚያሳይ ስትራቴጂካዊ ተቋማዊ መረጃ (Organizational Overview) ለአዲሱ ዋና ዳይሬክተሩ ቀርቧል።

በተለይም በየምክትል ዋና ዳይሬክተሮቹ ሥር የሚገኙ ዳይሬክቶሬቶች ስላሉበት ወቅታዊ የሥራ አፈጻጸም፣ የሥራ ፍሰትና አጠቃላይ የአሠራር ሁኔታ ዝርዝር ገለጻ ተደርጎላቸዋል።

ኢንጂነር ሽመልስ እሸቱ የቀረበውን ተቋማዊ መረጃ ካደመጡ በኋላ ለማኔጅመንት አባላቱ የሥራ መመሪያና ቀጣይ አቅጣጫዎችን ሰጥተዋል። ዋና ዳይሬክተሩ ባስተላለፉት መመሪያ፤ ይህንን አንጋፋ ተቋም ይበልጥ በማዘመን አዳዲስ መንገዶችን በመገንባት፣ ነባሮቹን በማጠናከርና በመጠገን ረገድ የላቀ ውጤት ማስመዝገብ እንደሚገባ አሳስበዋል።

አያይዘውም የፕሮጀክቶችን ጥራት ማረጋገጥ፣ በተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብና በጀት እንዲጠናቀቁ የቅርብ ክትትልና ቁጥጥር ማድረግ፣ እንዲሁም የውስጥ አሠራር ቅንጅትን ማጠናከር ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች መሆን እንዳለባቸው ጠቁመዋል። የተቋሙን ስኬታማ ጉዞ አጠናክሮ ለማስቀጠልም መላው የማኔጅመንት አባላትና የሥራ ኃላፊዎች በቁርጠኝነትና በከፍተኛ ኃላፊነት እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።

ዋና ዳይሬክተር ሆነው የተሾሙት ኢንጂነር ሽመልስ እሸቱ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሲቪል ኢንጂነሪንግ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን (BSc) ያገኙ ሲሆን፣ በተመሳሳይ ተቋም በኮንስትራክሽን ቴክኖሎጂ ማኔጅመንት የሁለተኛ ዲግሪያቸውን (MSc) አግኝተዋል። ወደዚህ ኃላፊነት ከመምጣታቸው አስቀድሞም የኢትዮጵያ ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽንን በዋና ሥራ አስፈጻሚነት በብቃት መምራታቸው ይታወሳል።

በተጨማሪ
› አጭር መልዕክት 8561
› ፖስታ ሳጥን ቁጥር 1770
› ድህረገጽ www.era.gov.et
› ፊስቡክ https://www.facebook.com/www.era.gov.et
› ቴሌግራም https://t.me/ethioroads
› ትዊተር https://twitter.com/EthiopiaRoadsAd
› ኢንስታግራም https://www.instagram.com/ethioroads
› ኢሜል communication@era.gov.et
› ዩቲዮብ www.youtube.com/@ethioroads